ሀገርን መገንባት የሚቻለው ህጻናት ላይ ሲሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ሀገር ተረካቢ ትውልድ መገንባት የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኬንያ ሞምባሳ ግዛት አስተዳዳሪ አብዱልስዋማድ ሸሪፍ ናስር እና ልዑክ ቡድናቸው ጋር ተወያይተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት÷ ሀገርን መገንባት የሚቻለው ህጻናት ላይ ሲሰራ እንደሆነና ለዚህም ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
ህጻናትን ለማሳደግ ምቹ እና ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ማድረግ የሚለውን ትልቅ ግብ ለማሳካት ጥናት ላይ የተመሰረተ ስርዓት በመዘርጋት ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
ለዚህም ለህጻናት እድገት ወሳኝ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል ከመቅጠር አንስቶ በርካታ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመው÷ በተቋማትም ለህጻናት ምቹ የሆነ ከባቢ እንዲፈጠር መሰረታዊ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ሀገር ተረካቢ ትውልድ መገንባት የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩንም ነው ከንቲባዋ የገለጹት።
የኬንያ ሞምባሳ ግዛት አስተዳዳሪ አብዱልስዋማድ ሸሪፍ ናስር በበኩላቸው÷ አዲስ አበባ የስበት ማዕከል እና የተቀናጀ ከተማ ተምሳሌት ሆና የምትጠቀስ መሆኗን ገልጸው፤ ከከተማዋ በርካታ ተሞክሮ እንደሚወስዱም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በተደረገላቸው ገለጻም በአዲስ አበባ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም እየተመራበት ያለው አግባብ የሚደነቅ መሆኑን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ልዑኩ በመዲናዋ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ አስተዳደር፣ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እንዲሁም የኮሪደር ልማት እና ሌሎች የከተማ ትራንስፎርሜሽን ስራዎችን በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርግ ተገልጿል።