15 ሚሊየን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ሆነዋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 15 ሚሊየን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ መሆናቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ ገለጹ፡፡
የአይዲ ፎር አፍሪካ-2025 ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የፋይዳ ስኬታማ አተገባበር ከቁጥር ባሻገር ለኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ወሳኝ የሆነውን የዲጂታል መሰረተ ልማት መገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር መኖር፣ የሀገር ውስጥ የመረጃ ስርዓት በመፍጠርና ባለሙያዎችን በማብቃት እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ጋር አጋርነትን በማጠናከር የተሰሩ ስራዎች ለተገኘው ውጤታማ አፈጻጸም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ብሔራዊ መታወቂያ ለሀገራዊ የልማት አጀንዳ ቁልፍ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ተግባራዊ በሆነባቸው ተቋማት አገልግሎት ለማቅረብ ይወስድ የነበረውን ጊዜ እስከ 60 በመቶ መቀነስ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
ጉባኤውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከአይዲ ፎር አፍሪካ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፥ ከ100 ሀገራት የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ልዑካን ይሳተፋሉ፡፡
ሲምፖዚየሞችና ወርክሾፖችን ባካተተው በዚህ ጉባኤ ላይ 35 የአፍሪካ ሀገራት የዲጂታል ማንነት ቴክኖሎጂ ልምድን እንደሚለዋወጡ ይጠበቃል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ