የምግብ ስርዓትን የሚያጠናክር የልምድ ልውውጥ አድርገናል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከብራዚል-አፍሪካ ጉባዔ ጎን ለጎን የምግብ ስርዓትን የሚያጠናክሩ የልምድ ልውውጥ መድረኮች መካሄዳቸውን ገለጹ፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ ልዑክ በ2ኛው የብራዚል-አፍሪካ የምግብ ዋስትና፣ ረሃብን መከላከል እና የገጠር ልማት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
መድረኩ የግብርና ምርት እድገት፣ የገጠር ልማትና የምግብ ዋስትና ማሻሻል ላይ ማተኮሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ግብርናን በተሻለ መንገድ የሚመሩ የጥናትና ምርምር፣ አዳዲስና በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን የሚያሳልጡ ተቋማት ግንባታ በዘርፉ ከፍ ያለ እመርታ ለማምጣት እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡
ጉባዔው ኢትዮጵያ በፖሊሲ የተደገፈ መሰረታዊ የለውጥ ስራዎችን በመተግበር ግብርናን ከፍ ባለ እመርታ ላይ ለማስገኘት የሰራችውና እየሰራች ያለው ተሞክሮ የሚቀርብበት ብሎም ከሌሎች ሀገራት ልምዶች የሚቀሰሙበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከጉባዔው ጎን ለጎን የዕውቀት ሽግግርና የደቡብ-ደቡብ ትብብርን በመጠቀም የምግብ ስርዓትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ የመስክ ምልከታዎች፣ የልምድ ልውውጦች እና ስምምነቶች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል፡፡
የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በበኩላቸው፥ የጉባዔው ዓላማ ጠንካራና ዘላቂ የምግብ ስርዓት ለመገንባት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ብራዚል ከአፍሪካ ሀገራት የምትማራቸውና የምታጋራቸው ተሞክሮዎች መኖራቸውን ገልጸው፥ እነዚህ የልምድ ልውውጦች ጠንካራ የምግብ ስርዓት ለመፍጠር ያስችላሉ ብለዋል፡፡
በፍሬህይወት ሰፊው