የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጉላት የኪነ ጥበብን አበርክቶ ማጠናከር ያስፈልጋል – ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጉላት የኪነ ጥበብን አበርክቶ ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ተናግረዋል።
ኪን ኢትዮጵያ – የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት የተሰኘ የጥበብ ጉዞ የሽኝት መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም አምባሳደሮችና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የኢትዮጵያን ጥበብ፣ ባህል እና ቋንቋ በማልማትና በማስተዋወቅ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል፡፡
በህብረ ብሔራዊ አንድነት የደመቀችውን ኢትዮጵያ አጉልቶ በመግለፅ ረገድ ጥበብ ያለውን አበርክቶ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ቱባ ባህል ለማስተዋወቅ መሰል መርሀ ግብሮች አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልጸው፤ ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ሂደትም አተይኬ ሚና እንደሚጫወቱ አመላክተዋል።
ከ50 በላይ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና ጥበብ የሚያሳይ የጥበብ ጉዞ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገርን ገፅታ የማስተዋወቅ ተግባር እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ዝግጅቱ የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊነት በፋሽን፣ በእደጥበብ እና ኪነጥበብ ለማስተዋወቅ ያለመ የመልቲሚዲያ መርሐ ግብር ነው ተብሏል።
በሄኖክ ኃይሉ