Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ሕብረት በሶሪያ ላይ የተጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ሊያነሳ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶሪያ የቀድሞ መሪ በሽር አል አሳድ ከስልጣን መውረድን ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረት በሶሪያ ላይ የተጣለውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለማንሳት ስምምነት ላይ መድረሱ ተሰማ፡፡

በሕብረቱ 27 አባል ሀገራት አምባሳደሮች የጸደቀው ይህ ውሳኔ፤ በአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፀድቆ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

በቅርቡ አሜሪካ በሶሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማቃለል የወሰደችው እርምጃ እና የሕብረቱ ውሳኔ፤ በሀገሪቱ የፋይናንስ መረጋጋትን እና መልሶ ግንባታን ለመደገፍ ዕገዛ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

በፈረንጆቹ 2012 እና 2013 በሶሪያ የባንክ፣ የትራንስፖርት እና የኢነርጂ ዘርፎች ላይ ያነጣጠሩ ማዕቀቦች ተጥለው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በመሆኑም አዲሱ ስምምነት፤ የሶሪያ ባንኮች በዓለም አቀፉ ሥርዓት ውስጥ እንዳይገቡ የሚገድበውን እና የሀገሪቱ የማዕከላዊ ባንክ ንብረቶች የሚያግደውን ውሳኔ ያነሳል፡፡

በአንጻሩ የጦር መሣሪያ ገደቦች እና ሌሎች ማዕቀቦች ባሉበት እንደሚቀጥሉ መገለጹን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

አዲሱ የሶሪያ መንግሥት፤ መብቶችን እና ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ማስከበር ካልቻለ ግን ማዕቀቡ ወደነበረበት ሊመለስ እንደሚችል የሕብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮች አስጠንቅቀዋል።

ውሳኔውን በደስታ እንደተቀበሉት የገለጹት የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል-ሻይባኒ፤ ለብሔራዊ መልሶ ግንባታ ብሎም ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ለመጋበዝ “ታሪካዊ ዕድል” መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.