Fana: At a Speed of Life!

ሲሚንቶ የማምረት አቅምን በዓመት ወደ 20 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማድረስ ተቻለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ሲሚንቶ የማምረት አቅምን በዓመት ወደ 20 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማድረስ መቻሉን የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ገለጹ፡፡

አራት የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ በማስገባት የሲሚንቶ አምራቾችን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የግብዓት አቅርቦት ምላሽ ለመስጠት በብረት፣ እምነ በረድ፣ ሲሚንቶና ሌሎች መስኮች ስኬታማ የምርታማነት አቅም እየተፈጠረ ነው ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያና ቻይና ባለሃብቶች አጋርነት በአጭር ጊዜ ማስፋፊያ የተገነባለት የፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካም ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርት ወደ ማምረት መሸጋገሩን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የነባር ፋብሪካዎችን ምርታማነት በማሳደግና አዳዲሶችን ወደ ሥራ በማስገባት ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለጎረቤት ሀገራት ሲሚንቶ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

የድሬዳዋ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው፤ ፓዮኔር ሲሚንቶ ከብክለት የጸዳ ቴክኖሎጂን ከመጠቀሙ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለከተማዋ ኢኮኖሚ መነቃቃት ጉልህ ሚና መወጣት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊዮን ዞን፤ ፋብሪካው አሁን ላይ ለ550 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን እና የማምረት አቅሙን በከፍተኛ መጠን ማሳደጉን አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.