የሚድሮክ አዋሽ ኮትድ ካልሺየም ካርቦኔት ግብዓት ማምረቻ ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል አዋሽ 7ኪሎ የተቋቋመው የሚድሮክ አዋሽ ኮትድ ካልሺየም ካርቦኔት ማምረቻ ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ የምርት ሂደት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አሕመድን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የዘመናዊ ህንፃ ኢንዱስትሪዎች የግል ማህበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አንዱዓለም ወ/ማሪያም እንደገለጹት፤ ፋብሪካው በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ ነው።
ፋብሪካው ለውሃ መስመር ቱቦዎች፣ ለፕላስቲክ ውጤቶች፣ ለጫማ ሶል፣ ለመድሃኒት፣ ለስፖንጅ እና ለኬብል ምርቶች ግብዓት የሚሆን ኮትድ ካልሺየም ካርቦኔት በተለያየ መጠን ያመርታል ብለዋል።
በዓመት 18 ሺህ ቶን ኮትድ ካልሺየም ካርቦኔት እንዲያመርት ሆኖ የተገነባው ፋብሪካው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ የማምረት አቅሙን 15 በመቶ ብቻ ተጠቅሞ እንደሚያመርት ገልጸዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በየዓመቱ ከግማሽ ቢሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ከውጭ ሀገር ይገባ የነበረውን 18 ሺህ ቶን ኮትድ ካልሺዬም ካርቦኔት በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የማምረት አቅሙ የ10 የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የግብዓት ፍላጎት ለመሸፈን ወደ ምርት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።
ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል የፈጠረው ፋብሪካው 97 በመቶ ግብዓት የሚያገኘው ከአካባቢው እንደሆነ ገልጸዋል።
በመራኦል ከድር