Fana: At a Speed of Life!

8 ነጥብ 9 ቢሊየን ሊትር ወተት ተመረተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2017 በጀት ዓመት ከገባ ጀምሮ እስካሁን ድረስ 8 ነጥብ 9 ቢሊየን ሊትር ወተት መመረቱን የኢትዮጵያ እንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዳኛቸው በየነ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት ሥራ ከተጀመረ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ሥራ በስፋት እየተተገበረ ነው።

ከብት በማርባት ሥራ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ለተሻሻለ ዝርያ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

በዚህም ዘንድሮ ወደ 3 ሚሊየን እንስሳቶችን የማዳቀል ሥራ መሰራቱን ጠቅሰው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ዝርያቸው የተሻሻለ ጥጆች ከመወለዳቸው ባለፈ የወተት ምርታማነት ላይ መጨመሩን ተናግረው፤ 8 ነጥብ 9 ቢሊየን ሊትር ወተት ተመርቷል ብለዋል።

ይህን ውጤት አጠናክሮ በማስቀጠል እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ምርቱን 10 ቢሊየን ሊትር በላይ ወተት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል።

የተሻለ ምርት ለማግኘት የመኖ አቅርቦት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ የተሻሻሉ የመኖ ዕፅዋቶችን የማልማት ሥራ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.