ጉባዔው አፍሪካ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየችበት ነው – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት ጉባዔ አፍሪካ ለዜጎቿ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየችበት መሆኑን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች አህጉራዊ ስብሰባ ዛሬ ሲጠናቀቅ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እንደገለጹት፤ ጉባኤው በዘርፉ ተግዳሮቶችና መልካም ዕድሎች ላይ በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል።
የሥራ ስምሪት መርሐ ግብሮችን ከሀገራዊ ልማት ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የጋራ አቋም የተቀመጠበት እንደሆነም አንስተዋል።
ጉባዔው የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የማህበራዊ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር ማዋሃድ በሚያስችሉ ስልቶች ላይ መምከሩን ገልጸዋል።
የአህጉሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች ላይ ጥልቅ ውይይት መደረጉንም ነው የተናገሩት።
ውይይቶቹ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በወረርሽኝ ማገገሚያ እና በፈጣን የከተሞች መስፋፋት እውነታዎች ላይ ማተኮራቸውን እንደገለጹ የዘገበው ኢዜአ ነው።
በተጨማሪም ችግሮቹን ለመቅረፍ በመንግስታት፣ በልማት ኤጀንሲዎች፣ በሲቪል ማህበራትና በግሉ ዘርፉ መካከል ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ መመላከቱን ተናግረዋል።
የዓለም ሥራ ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ፋንፋን ሩዋንዪንዶ ካዪራንጉዋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ስኬታማ ጉባኤ ማካሄዷን ጠቅሰው፤ ለኢትዮጵያ መንግሥትም ምስጋና አቅርበዋል።
ጉባኤው ከዚህ ቀደም ከተደረጉት የተሻለ ተሳታፊዎች የተገኙበት እንደሆነ ተናግረው፤ 30 ሚኒስትሮች፣ ሁለት ሺህ ተሳታፊዎች እና 50 ሀገራት የታደሙበት ነው ብለዋል።
20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት ስብሰባ አፍሪካ ለዜጎቿ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየችበት እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ዛምቢያ 21ኛውን የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች አህጉራዊ ጉባኤን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።