ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ የሰጠችው ትኩረት የተሻለ ውጤት ያመጣል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቴክኖሎጂ ዘርፍ የኢትዮጵያን አቅም ለማሳየት መንግስት ለቴክኖሎጂ ዘርፍ ትኩረት መስጠቱ ኢትዮጵያ ዲጂታል ከባቢ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚያጠናክር የዘርፉ ምሁራን ገለፁ፡፡
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ተመስገን መንግስቱ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ እየተተገበረ በሚገኘው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ስኬቶች ተመዝግቧል።
ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ እና በመጠቀም ረገድ በመንግስት በኩል እየተሰራ ያለው ስራ መልካም መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ኢንፎርማቲክስ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ አቶ ደስታ ዳና በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የሳበ እና በሁላችንም መዳፍ ላይ የሚገኝ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር በቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ እና ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱ የአገልግሎት መሻሻል ላይ ሚናው የጎላ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
የሀገራት እድገት በአብዛኛው መሠረት ያደረገው ቴክኖሎጂ እንደሆነ ጥናቶች እና ነባራዊ ሁኔታዎች ያስረዳሉ የሚሉት ምሁራኑ፤ ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት የተሻለ ውጤት የሚያመጣ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ ቴክኖሎጂ የምርጫ ጉዳይ አይደለም በማለት ገልጸው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራ በመሥራት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡
በኢብራሂም ባዲ