ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ አጀንዳዎች ስኬት የምታደርገውን ጥረት እንደምታጠናክር አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ በሁሉም መስክ ራሷን ለመቻል የያዘቻቸው ግቦች እንዲሳኩ አህጉራዊ ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለፁ።
የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት የተመሰረተበት 62ኛ ዓመት የሚታወስበት የአፍሪካ ቀን በዓል “ታሪካችንን መቃኘት ነገን ማስተካከል” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
በአከባበሩ ላይም፤ የሕብረቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ወጣቶች እና ሴቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ሚኒስትር ዴዔታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የቀደሙት አፍሪካውያን አባቶች የጋራ ራዕይ በማንገብ የአፍሪካ አንድነት እውን እንዲሆን ድርጅቱን በመመስረት ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ከፍተዋል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራቾችን ራዕይ ለማሳካት በትጋት መስራት እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሰላማዊ እና የተባበረች አፍሪካን እውን ለማድረግም በትብብር መስራት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
የአፍሪካን የፍትህ ጥያቄ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የአፍሪካን አጀንዳ ለስተጋባት የአፍሪካዊያን ዳያስፖራዎች ጥረት እና ህብረት ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚ ራስን መቻል ሌላው ቁልፍ አጀንዳችን ሊሆን ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው፤ በዚህ ረገድ የአህጉሪቷ ነጻ ንግድ ቀጣና ኢኒሼቲቭ ትልቅ የትብብር መሰረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዲጂታል ዘርፍ አፍሪካን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ ሌሎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያም አህጉራዊ አጀንዳዎች እንዲሳኩ የምታደርገውን ተሳትፎ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር መሀመድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው፤ በየመስኩ የአፍሪካን ብልጽግና የሚያጎናጽፉ ለውጦች እየመጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝን ጨምሮ በፈተና ውስጥም ተሞክሮ የሚሆን ዕድገት ያስመዘገቡ የአፍሪካ ሀገራት መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህን ተሞክሮ ማስፋት እንደሚገባም መክረዋል፡፡
አፍሪካውያን በምርቶቻቸው ላይ እሴት በመጨመር እና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ መረባረብ አለብንም ነው ያሉት፡፡