የትግራይ ሕዝብ በቀድሞ የሕወሓት ጥቂት አመራር አባላት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ መስዋዕትነት የሚከፍል አይደለም- አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ሕዝብ በቀድሞ የሕወሓት ጥቂት አመራር አባላት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመታለል መስዋዕትነት የሚከፍል አይደለም ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የትግራይ ሕዝብ የጥቂት ስልጣን ፈላጊ ቡድኖችን ድምጽ እየሰማ ለዓመታት ተጉዟልል፤ ከዚህ በኋላ በሐሰት ፕሮፖጋንዳ የሚታለል የለም፡፡
ሕዝቡ ሐሳቡን በነፃነት መግለጽ የጀመረው የጊዜያዊ አስተዳደር ከተመሰረተ በኋላ መሆኑን በመጥቀስ፤ ሕዝቡ የሰላም አካል መሆኑን የሚያረጋግጥበት መድረክ በየጊዜው ይዘጋጃል ነው ያሉት፡፡
የትግራይ ሕዝብ የተወሰኑ ሰዎችን የስልጣን ጥም ለማርካት መሞት የለበትም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የጥቂት ሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት የሚከፈል መስዋዕትነት አይኖርም ብለዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ አጀንዳ ሰላም መሆኑን ገልጸው፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ላይ በጋራ መምከር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡