የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦት ተደራሽነትን ማሳደግ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦት ተደራሽነትን መቶ በመቶ ለማድረስ እየሠራ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) እንዳሉት፤ በዚህ ዓመት የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦት ተደራሽነትን 72 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ነው፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦትን ለ17 ሚሊየን ሕዝብ ተደራሽ መደረጉን ጠቅሰው፤ በፈረንጆቹ 2030 ለማኅበረሰቡ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ እንዲሆን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ከበጀት ባሻገር ብድር በመውሰድ ጭምር የማኅበረሰቡን የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦት ችግር የሚቀርፉ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት እንደ ሀገር 205 ትምህርት ቤቶች የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦት በግቢያቸው እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ያልገቡ የውኃ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ