Fana: At a Speed of Life!

ኢንሳ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች በሳይበር ስልጠና ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የ2017 ዓ.ም የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ላይ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኢንሳ ላለፉት ሦስት ተከታታይ አመታት በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች በማሰልጠን ወደ ተቋሙና ወደ ሳይበር ኢንዱስትሪው እንዲቀላቀሉ አድርጓል፡፡
ዘንድሮ ለ4ኛ ዙር በመላ ሀገሪቱ ከአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እስከ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን በመመልመል ለማሰልጠን ዝግጅት መደረጉን በተቋሙ የሳይበር ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በየነ ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሰረት በሳይበር ደህንነት፣ በኢምቤድድ ሲስተም፣ በኤሮስፔስና መሰል ዘርፎች ላይ ልዩ ተሰጥኦና ፍላጎት ያላቸው በ www.talent.insa.gov.et ላይ እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
እስካሁን 500 የሚደርሱ ተማሪዎችን በሰመር ካምፕ ስልጠና ማብቃት እንደተቻለ ገልጸው፥ ነገር ግን ዓለም ከሚፈልገው የዘርፉ ሙያተኞች ቁጥር አንፃር ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ አንስተዋል።
ወጣቶችና ታዳጊዎች ላይ መስራት ወሳኝ በመሆኑ በሃገር አቀፍ ደረጃ ተሰጥኦና ፍላጎት ያላቸው ከ11 አመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎችም በምልመላው እንደሚካተቱ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የሀገርን የሳይበር ሉአላዊነት የሚያስከብሩ ወጣቶችን ለማፍራት የሰመር ካምፕ ስልጠና የላቀ አበርክቶ እንዳለው የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ በተለይም የ5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠናን የወሰዱ ታዳጊዎች ተቀባይነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በማህሌት ካሳሁን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.