Fana: At a Speed of Life!

የቡና ምርት መጠንን ለማሳደግ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡና መጠንን በማሳደግ አርሶ አደሩ፣ ላኪው እና ሀገር በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን የቡናናሻይ ባለስልጣን ገልጿል፡፡

ለዚህም የቡና ዘርና ችግኝ በማዘጋጀት አርሶ አደሩን የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታጋይ ኑሩ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም፤ 8 ሺህ 453 ኩንታል የቡና ዘር፣ 2 ቢሊየን 956 ሚሊየን 906 ሺህ 846 የቡና ችግኝ እንዲሁም 5 ሚሊየን 704 ሺህ 291 ቶን ኮምፖስት ለአርሶ አደሩ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

342 ሺህ 100 ኪሎ ግራም ፖሊቲን ቲዩብ፣ 2 ሺህ 231 የእጅ ጋሪ ፣ 220 አካፋ፣ 220 ባለሞተር የችግኝ ጉድጓድ መቆፈሪያ እና ባለሞተር መጎንደያ መጋዝ 225 ለቡና አምራች ወረዳዎች ተሠራጭቷል ብለዋል፡፡

100 ሺህ የቡና ችግኝ ከሚዛን ቴክኒክና ግብርና ኮሌጅ እና 1 ሚሊየን የቡና ችግኝ ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በፕሮጀክት ግዥ ተፈጽሞ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሮች መሠራጨቱንም ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም 1 ሺህ 450 ኪሎ ግራም የተሻሻሉ 19 ዓይነት ዝርያዎች ከጅማ ምርምር ማዕከል በፕሮጀክት በመግዛት ለቡና አልሚ አርሶ አደሮች ተሠራጭቷል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም፤ በ111 ሺህ 790 ሔክታር ላይ የቡና ጉንደላ፣ በ59 ሺህ 699 ሔክታር ላይ የቡና ነቅሎ ተከላ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የቡና ምርታማነት መጠን በሔክታር 8 ነጥብ 91 ኩንታል መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት አሥር ወራት 210 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ፤ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ከ50 እስከ 60 ለሚሆኑ ሀገራት ቡና የምትልክ ሲሆን፤ አሁንም የቡና መዳረሻዋን ለማስፋት እየተሠራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.