በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ12ኛ ክፍል ፈተና የማለፍ ምጣኔን የሚያሳድጉ ተግባራት ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ12ኛ ክፍል ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና የማለፍ ምጣኔን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትልና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ማልደዮ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ ዘንድሮ 35 ሺህ 246 የክልሉ ተማሪዎች ሀገር አቀፉን የ12ኛ ክፍል ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ይወስዳሉ።
ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል 7 ሺህ 211 ያህሉ ፈተናውን በበይነመረብ እንደሚፈተኑ ጠቁመው፤ ተማሪዎቹ ስለ ፈተና አሰጣጡ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በወረቀት የሚፈተኑ 28 ሺህ 35 ተማሪዎች ደግሞ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ልምምድ እያደረጉ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የ12ኛ ክፍል ፈተና የማሳለፍ ምጣኔ መቀነሱን አስታውሰው፤ ችግሩን ለመፍታትና ምጣኔውን ለማሳደግ በዳሰሳ ጥናቶች የተደገፈ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በ2015 ዓ.ም ከነበረው 2 ነጥብ 7 በመቶ የማሳለፍ ምጣኔ በ2016 ዓ.ም ወደ 3 ነጥብ 4 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህ ዓመት የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚያስችል ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም ከትምህርት ቤት እስከ ክልል ድረስ የሚመለከታቸውን አካላት በሙሉ በማሳተፍ ምክክር እና የትምህርት ቤቶች አመራር ሪፎርም መደረጉን አመልክተዋል።
እንዲሁም በክልሉ ከሚገኙ የወልቂጤ፣ ወራቤ እና ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።
የመማር ማስተማር ሂደቱ በወቅቱ በመጀመሩ አሁን ላይ የትምህርት ይዘቶችን በመጨረስ ተማሪዎች ለፈተናው የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት