የኮንፈረንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ይደረጋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንግሊዙ ክለብ ቼልሲ ከስፔኑ ሪያል ቤቲስ ጋር የሚያደርጉት የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4 ሠዓት ላይ በፖላንድ ታርዚኒስኪ አሬና ስታዲየም ይደረጋል፡፡
በሪያል ቤቲስ በኩል በማንቼስተር ዩናይትድ ስኬታማ ጊዜ ያላሳለፈው እና በጥር የዝውውር መስኮት ቡድኑን የተቀላቀለው አንቶኒ እንዲሁም የሪያል ማድሪድ የቀድሞ አንጋፋ ተጫዋች ኢስኮ ጥምረት ለቼልሲ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ቼልሲ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ ብቸኛው አራቱንም የአውሮፓ ዋንጫዎች ያነሳ ቡድን ለመሆን ይፋለማል፡፡
ሪያል ቤቲስ በበኩሉ የኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት የሚያደርገው ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ክለቦች በፈረንጆቹ 2005 በሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ሁለት ጊዜ መገናኘታቸው እና አንድ አንድ ጊዜ መሸናነፋቸው ይታወሳል፡፡
በአቤል ንዋይ