Fana: At a Speed of Life!

በማድሪድ ትልቅ የቤት ሥራ የሚጠብቀው ዣቢ አሎንሶ….

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዣቢ አሎንሶ በሪያል ማድሪድ፣ በሊቨርፑል እንዲሁም ባየርን ሙኒክ ቤት በተጫዋችነት ዘመኑ ብቃቱን ያስመሰከረ ስኬታማ የመሐል ሜዳ ተጫዋች ነበር፡፡

ከፈረንጆቹ 2009 እስከ 2014 ድረስም በሪያል ማድሪድ ቤት በተጫዋችነት አሳልፏል፡፡

በማድሪድ ቆይታው 236 ጨዋታዎችን በማድረግ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እና የስፔን ላሊጋ ዋንጫን ጨምሮ በርካታ ዋንጫዎችን ከፍ አድርጓል፡፡

እንዲሁም ከእንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል ጋር በፈረንጆቹ 2005 የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አሳክቷል፡፡

ከጀርመኑ ክለብ ባየር ሙኒክ ጋር በነበረ ጊዜም ለሦስት ተከታታይ የውድድር ዓመታት የቡንደስሊጋ ዋንጫ አንስቷል፡፡

ወደ አሰልጣኝነት ሥራ ሲገባም የሪያል ማድሪድ አካዳሚ ቡድንን በማሰልጠን የጀመረ ሲሆን፤ ከዚያ በመቀጠል የሌላኛውን የስፔን ክለብ የሪያል ሶሴይዳድን ሁለተኛ ቡድን ለሦስት ዓመታት አሰልጥኗል፡፡

ከስፔን ወደ ጀርመን በማቅናት ባየር ሊቨርኩሰንን በዋና አሰልጣኝነት ተርክቦ ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡

በዚሁ ወቅትም ሙኒክ ለ11 ዓመታት ያለተቀናቃኝ ሲያነሳው የነበረውን የጀርመን ቡንደስሊጋ ዋንጫ፤ በ2023/24 የውድድር ዓመት በባየር ሊቨርኩሰን ቆይታ በማሳካት ታሪክ ጽፏል፡፡

ባየር ሊቨርኩሰኖች ይህንን ደስታ ላጎናፀፋቸው አሰልጣኝ ያላቸውን ክብር ለመግለጽ ወደ ስታዲየማቸው የሚወስደውን መንገድ በዣቢ አሎንሶ ስም መሰየማቸውም አይዘነጋም፡፡

ከዚህ ሁሉ የሥራ ሕይወት በኋላ ሊቨርፑል እና ማንቼስተር ዩናይትድን ጨምሮ የተለያዩ ክለቦች እሱን አሰልጣኝ ለማድረግ ጥረዋል፡፡

በመጨረሻም መዳረሻው የቀድሞ ቤቱ ሪያል ማድሪድ ሆነ፤ ሲጠበቅ እንደነበረው ጣልያናዊውን አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲን ተክቶ ሳንቲያጎ ቤርናባው ደረሰ፡፡

ሪያል ማድሪድ በዚህ የውድድር ዓመት በምንጊዜም ተቀናቃኙ የካታላኑ ክለብ ባርሴሎና የበላይነት ተወስዶበት የውድድር ዘመኑን ጨርሷል፤ የእሱ ነው በሚባልለት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግም በደርሶ መልስ በአርሰናል ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበቱ ይታወሳል፡፡

የማድሪድ አሰልጣኝ ዣቢ አሎንሶ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በባርሴሎና የተወሰደበትን የበላይነት ማስመለስ እና ክለቡን ወደ ሚታወቅበት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የበላይነት ለመመለስ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል፡፡

በወንድማገኝ ፀጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.