Fana: At a Speed of Life!

የሰመር ካምፕ ሰልጣኞች ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን መስራት ችለዋል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የሰመር ካምፕ ስልጠና የወሰዱ አዳጊዎች ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን መስራት ችለዋል።

ሰልጣኞቹ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ባገኙት ስልጠና የሳይበር ምንተፋን ለመከላከል የሚያስችል በቂ እውቀት አግኝተዋል።

ስልጠናው የሳይበር ደህንነትን የሚያረጋግጡ አዳዲስ ሶፍትዌሮችን በማበልፀግና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በመስራት ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

አዳጊዎቹ ከሰሯቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል ጠጥቶ በማሽከርከር የሚመጣ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል፣ የአካባቢ ፅዳትን ለማስጠበቅና ብክለትን ለመከላከል የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይጠቀሳሉ፡፡

እንደሰልጣኞቹ አስተያየት፤ ስልጠናው ኪሂሎትን ከማሳደግም ባለፈ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥንካሬንም አግኝተውበታል።

የሰመር ካምፕ ስልጠና መርሐ ግብር 20 በመቶ ስልጠና የሚከታተሉበት ሲሆን፥ ቀሪው 80 በመቶ ደግሞ የራሳቸውን ተሰጥኦ የሚፈትሹበት ሙከራ ነው።

በስልጠናዎቹ ተሳትፈው ብቁ የሆኑት አዳጊዎች እና ወጣቶች መደበኛ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ የሥራ ዕድል እያገኙና የራሳቸውንም ሥራ እየፈጠሩ ነው።

የኢንሳ የሳይበር ልሕቀት ማዕከል ዳይሬክተር ቢሻው በየነ የዘንድሮ የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ሰመር ካምፕ ስልጠና ሐምሌ 1 ይጀምራል ብለዋል።

በማህሌት ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.