Fana: At a Speed of Life!

የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎችን የሚያካትተው ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን…

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁሉንም የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች የሚያካትተው የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ነው፡፡

የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሞቱማ ተመስገን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ባህልና ወግን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ፣ የንግድ፣ የቴክኖሎጂና የኢንቨስትመንት ከተማ ነው።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመሠረታዊነት የመለወጥ ርዕይን ሰንቆ የተመሰረተው የኢኮኖሚ ዞኑ÷ለአንድ ከተማ ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን እየዘረጋ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በአዳማ እና ሞጆ ከተሞች መካከል እየተገነባ የሚገኘው ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ለኢንዱስትሪና ለኑሮ ምቹ እንዲሆን ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ሁሉንም የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች እንደሚያካተት ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው÷የውጭና የሀገር ውስጥ ገበያዎች ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች በሰፈራና በወታደራዊ ካምፖች ላይ ተመስርተው መቆርቆራቸውን አስታውሰው ፥ ገዳ ግን በኢኮኖሚ ላይ ተመስርቶ እየተገነባ ያለ ዘመናዊ ከተማ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ የመብራት፣ የመንገድ፣ የውሃ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እየተሟሉ ሲሆን ፥ 28 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 18 ባለሃብቶች ሥራ ጀምረዋል።

በቅርቡ 10 ተጨማሪ ባለ ሃብቶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ሞቱማ ÷ እስካሁን ለ1 ሺህ 90 ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን አጠቃላይ ግንባታ 24 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን÷ የመጀመሪያው ምዕራፍ በ3 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ይገኛል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ እንዲሁም አጠቃላይ ግንባታውን ደግሞ በቀጣይ 40 ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱ ተጠቅሷል፡፡

በሲፈን መገርሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.