ከ55 ተቋማት ጋር የፋይዳ መታወቂያን የማስተሳሰር ሥራ ተሰርቷል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋይዳ መታወቂያን ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ለማስተሳሰር በተደረገው ጥረት እስካሁን ከ55 ተቋማት ጋር የፋይዳ መታወቂያን የማስተሳሰር ሥራ ተሰርቷል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት የስትራቴጂክ ግንኙነት ኃላፊ አቤኔዘር ፈለቀ እንዳሉት÷ በሁሉም ክልሎች የዲጂታል መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም ከ1 ሺህ በላይ በሆኑ ጣቢዎች የፋይዳ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን አንስተው÷ በክልሎች የኢትዮ ቴሌኮምና ገቢዎች ቢሮዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
በቀጣይ በባንኮች አማካይነት ተጨማሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የምዝገባ ማሽኖችን የማስገባት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል።
እስካሁን ከ55 ተቋማት ጋር የፋይዳ መታወቂያን የማስተሳሰር ሥራዎች መሰራቱን ገልጸው÷ በቀጣይነትም ከተለያዩ የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ከ15 ሚሊየን 991 ሺህ በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማካሄዳቸውን ጠቅሰው÷ ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ ለማድረግ በዘመቻም ጭምር ግንዛቤን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው።
በአድማሱ አራጋው