ደቡብ ዕዝ ሀገራዊ ግዳጁን በብቃት እየተወጣ ነው – ሜ/ጄ አድማሱ አለሙ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሠራዊት ደቡብ ዕዝ ሀገራዊ ግዳጁን በብቃትና ጀግንነት እየተወጣ ነው አሉ የዕዙ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄነራል አድማሱ አለሙ፡፡
ሜጀር ጄነራል አድማሱ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ደቡብ ዕዝ የሠራዊቱን ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም ሠራዊቱ ሀገራዊ ተልዕኮውን በሚገባ እንዲወጣ በሥነ ልቦና፣ በአካላዊ ብቃት፣ በወታደራዊ ሳይንስና ዲሲፒሊን እየታነጸ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ዕዙ በሚንቀሳቀስባቸው ቀጣናዎች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ሃይሎች ላይ አስፈላጊውን ርምጃ በመውሰድ አሁን ላይ የሰላም አየር እንዲነፍስ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ሠራዊቱ የትኛውንም ጥቃት መመከት የሚያስችል ቁመና ላይ ነው ያሉት ምክትል አዛዡ÷ ሁለንተናዊ አቅምን የማሳደጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡
ከታሪካዊ ጠላቶች አፍራሽ ተልዕኮ በመቀበል ኢትዮጵያ የጀመረችውን ልማት ለማደናቀፍ የሚሰሩ ሃይሎችን አንታገስም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ