ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጣቸው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀረሪ ክልል ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 67 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።
የክልሉ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ቢሮ ኃላፊ ኢስማኤል ዩሱፍ በክልሉ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ለባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን ፍቃድ ወስደው ለዓመታት ሳያለሙ በቆዩ 131 አልሚዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 29 ባለሃብቶች መሬት በምደባ መካሄዱን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል እንደሀገር ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማነቃቃትና ተኪ ምርቶችን በማምረት ረገድ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።
በዚህም ተዘግተው የቆዩ በርካታ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በሦስቱ የገጠር ወረዳዎች የአትክልትና ፍራፍሬ እና የማዕድን ዘርፍን ጨምሮ የየአካባቢውን ፀጋ መሰረት ባደረገ መልኩ ስድስት ኢንዱስትሪዎችን ለመክፈት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዘርፉም ከ6 ሺህ 100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አቶ ኢስማኤል ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።
በተስፋዬ ኃይሉ