ድንች ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያለውን ሚና የሚመጥን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ድንች ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያለውን ሚና የሚመጥን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪዎች ጠየቁ።
የድንች ምርት ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አበርክቶው የጎላ መሆኑን የግብርና ዘርፍ ተመራማሪዎች ያነሳሉ።
በኢትዮጵያ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ድንችን በሰርክ አመጋገብ ውስጥ በተለያየ ሁኔታ ይጠቀማል።
ድንች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋም የሚችልና በውስን ቦታና በአጭር ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ተመራማሪዎቹ ያስረዳሉ።
አይሪሽ ፖቴቶ የምርምርና ልማት ማህበር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር 2ኛውን ዓለም አቀፍ የድንች ቀን አክብሯል።
ለበርካታ ዓመታት በድንች ላይ ምርምር ሲያከናውኑ የቆዩት አቶ ገብረመድህን ወልደጊዮርጊስ በዚሁ ወቅት፥ ድንችን ከተለምዷዊ አመጋገብ ባለፈ በተለያዩ መንገዶች ለምግብ የመጠቀም ሁኔታ እየተዘወተረ ነው ብለዋል።
ድንች ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦና ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው አንጻር በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠውም ተናግረዋል።
የዓለም አቀፍ ድንች ምርምር ተቋም የኢትዮጵያ ቢሮ ተጠሪ ሰጠኝ ገበየሁ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥናት ድንች በተለይም ለምግብ ዋስትና ስትራቴጂያዊ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም በገጠሩ ክፍል የእህል ክምችት በሚያልቅበት የክረምት ወቅት ሁነኛ የምግብ አማራጭ መሆኑን በመጥቀስ ለምግብ ዋስትና ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ድንችን በአግሮ ፕሮሰሲንግ በችብስ መልክ የማቅረብ ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውን የሚገልጹት ተመራማሪዎቹ፤ ሆኖም ዘርፈ ብዙ አበርክቶውን የሚመጥን ትኩረት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል፡፡
በአጭር ጊዜና በውስን ቦታ ከፍተኛ መጠን ያለው የድንች ምርት ማግኘት እንደሚቻል ገልጸው፥ የተሻሻሉ ዝርያዎችንና የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በማሳደግ ዘርፉን ማገዝ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በድንች ላይ በርካታ ምርምሮችን በማድረግ የተሻሻሉ ዝርያዎች ማቅረቡን በተቋሙ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ፍቃዱ ጉርሙ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የድንች ምርት በግብርና ዘርፉ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት ለኢኮኖሚና ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያለውን አስተዋጽኦ ማሳደግ እንዲቻል የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ማመላከት እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
አርሶ አደሩ ከድንች ምርት ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዳያገኝ በገበያ ሰንሰለቱ ያሉ አሰራሮችን መፈተሽና ማስተካከል እንደሚገባም በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡
አርሶ አደሮች በድንች ምርት ሂደት 60 በመቶ ገደማ ወጪ የሚያወጡ ቢሆንም በገበያ ሰንሰለቱ ባለው ክፍተት ምክንያት ከሽያጩ የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ ግን ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ሰጠኝ ገበየሁ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥናት አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በበኩሉ፥ በገበያው ሰንሰለት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የገበያ አማራጮች ላይ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡
ድንች ከምርት ሂደት ጀምሮ ባሉ ሂደቶች በርካታ የሰው ኃይል ተሳትፎን የሚጠይቅ መሆኑን ተከትሎ በዘርፉ ይበልጥ መስራት ከተቻለ በስራ እድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመድረኩ ላይ ተመላክቷል፡፡
ለድንች ምርት ይበልጥ ትኩረት በመስጠት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መሙላትና ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ