በሚያዝያ እና ግንቦት ወራት በሀገር ውስጥ ትርጉም ያላቸው ርምጃዎች ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሚያዝያ እና ግንቦት ወራት በሀገር ውስጥ ትርጉም ያላቸው ርምጃዎች የተከናወኑበት ነው አለ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚያዝያ/ግንቦት 2017 ወር በኢኮኖሚ ልማት፣ ቴክኖሎጂ እድገት፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እና ሀገራዊ ልማት አንፃር የመንግሥታቸውን ፅኑ አቋም የሚያሳዩ ተከታታይ ተግባራት ማከናወናቸውን የጽሕፈት ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
የወሩ ተግባር በ44ኛው የሚኒስትሮች ምክርቤት መደበኛ ስብሰባ የጀመረ መጀመሩን የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፤ ቁልፍ የሆኑ ሀገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ውይይት እንደተደረገባቸው አንስቷል፡፡
ከዚያም በመቀጠል የኢትዮጵያ ታምርት 2017 ኤክስፖ በይፋ የተከፈተ ሲሆን ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት በተከናወነው በዚህ ኤክስፖ፤ 288 ሀገር በቀል አምራቾች በማደግ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ የአምራች ዘርፍ ምርቶች አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻ ንግግራቸው የኢኮኖሚ ሽግግርን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተው ያነሱ ሲሆን፤ የሀገር መረጋጋት ከኢኮኖሚ መዘመን ውጭ ሊሳካ እንደማይችል ገልፀዋል።
ዘንድሮ የሚጠበቀውን 12 በመቶ ዕድገት ጨምሮ በዘርፉ የሚጠበቀውን እድገት በማንሳትም የማምረት አቅምን በአግባቡ የመጠቀም ልምምድ መጨመሩን እና የገቢ መጨመርን አውስተዋል።
መንግሥት በግብርና እንደ አግሮ ፕሮሰሲንግ ቴክኖሎጂ የማዘመንን እና ፈጠራን የማበልፀግን ሥራ ቅድሚያ እንደሰጠም በወቅቱ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቴክኖሎጂ እና በዲጂታል ልማት ዘርፍም በ”አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለአፍሪካ” መርሐ ግብር የ”ቴክኤክስፖ 2025” ላይ ቁልፍ ንግግር አቅርበዋል።
አፍሪካ ሥነ ምግባርን በጠበቀ፣ አካታች እና ዘላቂነት ባለው የራሷ መንገድ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን መፃኢ እድገት ቅርፅ የመስጠት እድል እንዳላት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
እንደ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፤ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም (ፋይዳ) እና የአምስት ሚሊየን ኮደርስ መርሐ ግብርን በማንሳት ኢትዮጵያ የዲጂታል እውቀት የጨበጠ የነገ ትውልድ በመገንባት ላይ ያላትን ሚና ገልጸዋል።
በወሩ አጋማሽም ኢትዮጵያ የ አይ ዲ 4 አፍሪካ (ID4Africa) 2025 ጉባኤን ያስተናገደች ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን የማሻገር አቅም አስረድተዋል::
በአሁኑ ወቅት ከ15 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በሥርዓቱ ያቀፈው ፋይዳ ከአሁኑ በፋይናንስ፣ በጤና እና ትምህርት ቁልፍ ዘርፎች በትሪሊየን ብር የሚቆጠር የዲጂታል ልውውጥ አመቻችቷል።
ከቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ’Tech Talk with Solomon’ የቃለምልልስ ቆይታም አድርገው ነበር።
በዚሁ ወርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ116ኛው ብሔራዊ የፖሊስ ቀን በዓልም የተገኙ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሊኖር ለሚገባው የቀጠለ ትብብር ጥሪ አቅርበው፤ የፖሊስን የሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት የመጠበቅ ኃላፊነት ደግመው አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ የግንቦት ወር ሌላው ትኩረት ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በፓሪስ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ተገናኝተው የሁለትዮሽ ስምምነቶችን አፈፃፀም ገምግመዋል።
እንደ ስቴሽን ኤፍ፣ ኖኪያ ፍራንስ እና የታሌ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ያሉ የቴክኖሎጂ ተቋማትን ጎብኝተው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ሳይበር ደኅንነት እና ቴሌኮሙኒኬሽን የታዩ ፈጠራዎችን ተመልክተዋል።
እነዚህ ጉብኝቶች ኢትዮጵያ የቀጣናው የቴክኖሎጂ መሪ ለመሆን ያላትን ፍላጎት ያረጋገጡ ነበሩ።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታደሰውን የኖትረዳም ካቴድራል ጎብኝተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ባሉ ብሔራዊ ቅርሶች ጥገና ሥራ በማከናወን ላይ ያለችውን የባሕል ጥበቃ ጽኑ አቋም እንቅስቃሴ ተገቢነት ያረጋገጠ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፈረንሳይ ቆይታቸው በመቀጠል ወደ ሮም አቅንተው በጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል የቆየውን የረጅም ዘመን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እና የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስፋት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ጣሊያን በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እና ልማት ዘርፍ ቁልፍ አጋር ሆና ቀጥላለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላም የኢትዮጵያ ስፔስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
በተቋሙ በሥራ ላይ ያለውን የዘመነ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የጂኦስፓሻል መረጃ ለሀገር አቀፍ እቅድ፣ ቅድመ ግምት እና የአደጋ ዝግጁነት ሥራ የሚውልበትን መንገድ ገምግመዋል።
ይህ ጉብኝት መንግሥት በሳይንስ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ እና በውሂብ መረጃ ላይ የተመሠረተ የአመራር ሥራ ለመከወን ያለውን አፅንኦት ያረጋገጠ ነበር።
በዚሁ ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዛት ያላቸው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ውይይቶችን አካሂደዋል።
የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የፕሬዚዳንት ጁአዎ ሎሬንቾን ልዩ መልዕክተኛ ቴቴ አንቶኒዮን ተቀብለዋል።
ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሳር ጋርም በተለያዩ መስኮች ትብብሮች በሚጠናከሩበት መንገዶች ላይ ተወያይተዋል።
በኳታር ሚኒስትር ዶክተር መሃመድ ቢን አብዱልአዚዝ አልካሊፊ አቅራቢነት ከኳታር አሚር የተላከውን መልዕክትም ተቀብለዋል።
በአጠቃላይ በሚያዝያ/ግንቦት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ዘርፎች ሰፋ ያሉ ክንውኖች ያካሄዱበት፣ በሀገር ውስጥ ትርጉም ያላቸው ርምጃዎች የተከናወኑበት፣ በዲጂታል እና ፈጠራ መስክ እመርታዎች የተመዘገቡበት ብሎም በዓለም አቀፍ መድረኮች ትብብሮች የተጠናከሩበት ወር ነበር።
ሁሉም ተግባራት ለኢትዮጵያ እድገት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የታለሙ ስኬታማ ክንውኖች ነበሩ ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡