Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ ሀገራዊ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግና ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባህልን ለማዳበር ሀገራዊ ምክክሩ የማይተካ ሚና አለው አሉ የፌደራል ተቋማትና ማኅበራት አጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ተሳታፊዎች።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማትና ማኅበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።

በእስከ አሁኑ ሂደትም 38 የፌዴራል ተቋማትና ማኅበራትን የወከሉ አጀንዳዎችን ለዋናው መድረክ አቅርበዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በኢትዮጵያ በየጊዜው ለሚከሰቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት የምክክር ባህልን ማዳበር ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ለትውልዱ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ የላቀ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ከገንዘብ ሚኒስቴር በውይይቱ የተሳተፉት ኃይሉ በጆ እንዳሉት፤ የማያግባቡ ሐሳቦችን በምክክር መፍታት የስልጣኔ ምልክት በመሆኑ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሁሉ በሀገር ጉዳይ በጋራ ለመምከርና የተሻለ ሀገር ለመገንባት የጀመሩት ምክክር ለዘላቂ ልማትና ብልጽግና ወሳኝ ነው።

የድሬዳዋ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ይፍቱ አባስ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የምክክር ባህልን ለማዳበርና ዜጎች ጥያቄ ሲኖራቸው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ማቅረብ እንዲችሉ መሰረት የሚጥል መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዮሴፍ አበራ በሀገር ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሁሉንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመግለጽ፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ጠቃሚ አጀንዳዎችን በማቅረብ የተሻለ ነገን መገንባት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የታሪክ ተመራማሪው አደም ካሚል (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ወጣቱ አባቶቹ ያስረከቡትን ገናና ሀገር ጠብቆና አበልጽጎ ለማቆየት ችግሮችን በሰከነ መንገድ የመፍታት ባህልን ሊያዳብር እንደሚገባ መክረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.