Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቂ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ4 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፡፡

የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ችግኝ የሚተከልበት 916 ሔክታር መሬት ተለይቷል፡፡

ከተለየው መሬት በተጨማሪ ቀደም ሲል ተከላ በተከናወነባቸው አካባቢዎች የሳሱ እና ሌሎች ቦታዎች ላይ ችግኝ እንደሚተከል ጠቁመዋል፡፡

የቦታ ልየታውን ተከትሎ አሁን በተለያዩ ወረዳዎች የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ መጀመሩን ገልጸው፤ ጉድጓዶቹ በሚፈለገው መስፈርት መሰረት እንዲቆፈሩ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

እስከ አሁን ድረስ ለተከላ የደረሱ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ዘንድሮ ከሚተከሉት መካከል፤ የውበት፣ የደን፣ የፍራፍሬ እና የቅመማቅመም ችግኞች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት መጠን 80 በመቶ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪ አረንጓዴ ዐሻራ ለትውለድ የሚሠራ ዘመን ተሻጋሪ ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ፤ ችግኞች ሊጸድቁ በሚችሉበት ሁኔታ በአግባቡ በመትከል እና በመንከባከብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.