የፌደራል ተቋማት እና ማኅበራት አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የነቃ ተሳትፎ ተመዝግቦበታል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ የፌደራል ተቋማት እና ማኅበራት አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የነቃ ተሳትፎ ተመዝግቦበታል አሉ።
ዛሬን ጨምሮ ላለፉት ሦስት ቀናት በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ላይ የነበሩት የፌደራል ተቋማት እና ማኅበራት አጀንዳቸውን ለዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)፣ ለምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ እና ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት አስረክበዋል።
የመርሃ ግብሩን መጠናቀቅ አስመልክቶ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ ባደረጉት ንግግር፤ የተቋማቱ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በስኬት ተጠናቋል ብለዋል።
በየደረጃው የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ የተመዘገበበት ነው በማለት ገልጸው፤ በአሳታፊ እና አካታችነቱ ምሳሌ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ሂደቱ እምነት የተጣለበት እንዲሆን ኮሚሽኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል።
የፌደራል ተቋማት እና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍም ሁሉንም ወገን ያሳተፈ መሆኑን አንስተው፤ የችግሩን ሥር ለመንቀል የምንሄድበትን መንገድ የሚያደናቅፍ ሂደት አይኖርም ብለዋል።
ይህንን መድረክ ጨምሮ እስካሁን የተካሄዱ 14 የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮች በምክክር ችግርን ለመፍታት እየተኬደ ያለውን መንገድ ማጋመሳችንን አመላካች ነውም ብለዋል ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ።
በይስማው አደራው