የነገዋ ኢትዮጵያችን በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንድትቆም ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮቿ ላይ እየመከረች ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የነገዋ ኢትዮጵያችን በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንድትቆም ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮቿ ላይ እየመከረች ነው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
አገልገሎቱ ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የጋራ ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ የሆኑ ችግሮቻቸውን በምክክር ለመፍታት ቆራጥ ርምጃ ወስደው የተነሡበት ወቅት ነው ብሏል።
መንግሥት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያከናውነዉን ምክክር በገለልተኝነት እንዲያከናውን የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጫው አረጋግጧል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-
“የነገዋ ኢትዮጵያችን በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንድትቆም ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮቿ ላይ እየመከረች ነው።”
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የጋራ ዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ የሆኑ ችግሮቻቸዉን በምክክር ለመፍታት ቆራጥ ርምጃ ወስደው የተነሡበት ወቅት ነው።
ሀገራችን በበርካታ ጉዳዮች በተቃርኖዎች ውስጥ ለረዥም ዘመናት ስትናጥ እና በአስከፊ ግጭቶች ውስጥ ስታልፍ ቆይታለች። በተለይም ለረዥም ዓመታት እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በፖለቲካ እና በሐሳብ መሪዎች እንዲሁም በኅብረተሰቡ ክፍሎች መካከል ልዩነት እና አለመግባባቶች ኖረዋል። እነዚህን አለመግባባቶች በየዘመኑ እየፈታን የመጣንበት መንገድ ዘላቂ ትምምን በሚፈጥር መልኩ ስላልነበረ ከጦርነት እና ግጭት አዙሪት በዘላቂነት መንጭቀን እንዳንወጣ እንዳረገን እሙን ነው።
እነዚህ የግጭት መንገዶች እጅግ በርካታ ውድመት አስከትለዋል። ለረጅም ጊዜ ይዘን የመጣነው ልምምድ እና ዝንባሌ ታላላቅ ሕልሞቻችንን በጋራ እንዳናሳካ እንቅፋት ሆኖብን ቆይቷል። እነዚህ መንገዶች አንዱ የጀመረው ላይ እየገነባን የምንሄድ ሳይሆን ሁሌም ከዜሮ ጀማሪዎች እንድንሆን፣ በተቋማት እና በመሠረታዊ የሀገር ምሰሶዎች ላይ እምነት፣ የጋራ የሆነ ሀገራዊ የተስፋ ዕይታ እንዳይኖረን አድርገውን ቆይተዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ ባለመምከራችን ያያያዙን፣ ያጋመዱን የተለያዩ ጥብቅ እሴቶቻችንን ለሚሸረሽሩ አካላት ምቹ ሁኔታ ስንፈጥር ኖረናል።
ይህን አዙሪት በዘላቂነት ለመፍታት ልዩነቶቻችንን እና አለመግባባቶችን ላይ ሰፋፊ ሀገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። ኮሚሽኑ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት፤ በሂደትም መተማመን ለማጎልበት ያለውን የማይተካ ፋይዳ በመገንዘብ ነጻ፣ ገለልተኛ እና አካታች እንዲሆን መንግሥት አስፈላጊውን ሕጋዊና መዋቅራዊ ድጋፍ አድርጓል።
በዚህም ላለፉት ሦስት ዓመታት ከሕጋዊ እና መዋቅራዊ ዝግጅቶች ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። በዐሥራ አንዱ የሀገራችን ክልሎች እና በኹለቱ ከተማ አስተዳድሮች በርካታ ባለድርሻዎችን እና ተሳታፊዎችን ያሳተፉ ውይይቶችን አከናውኗል፤ በቀረዉ የትግራይ ክልልም ምክክሩን ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ባለፉት ዐሥር ወራት ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ ተወያይተዋል፤ ተመካክረዋል።
አሁንም 14ኛዉ የፌዴራል ተቋማት እና ማኅበራት የምክክር እና አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክም በአዲስ አበባ ተካሂዶ በስኬት ተጠናቋል። በመድረኩ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ማኅበራት እና ተቋማት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪና የማኅበረሰብ አንቂዎቸ፣ የዲሞክራሲ እና የሃይማኖት ተቋማት፣ የፀጥታና ደኅንነት አካላት፣ የሚዲያ ተቋማት እንዲሁም የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች ናቸው። አጀንዳዎቹ በተለያዩ ዘርፎች ተደራጅተው የቀረቡ ሲሆን በቀጣይ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የተነሡ አጀንዳዎች ላይ ምክክር ይቀጥላል።
መንግሥት ኮሚሽኑ የሚያከናውነዉን ምክክር በገለልተኝነት እንዲያከናውን የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት
ግንቦት 24 ቀን 2017 ዓ/ም