በኦሮሚያ ክልል የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 61 በመቶ ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ወደ ውጪ ከተላኩ ምርቶች 837 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል አለ የክልሉ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ አሕመድ ኢድሪስ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አገልግሎት አሰጣጥ ምቹና ተደራሽ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡
ኢንቨስትመንት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ የክልሉን እምቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በክልሉ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ከማስፋት ባለፈ የውጪ እና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ አስፈላጊው የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የኢንቨስትመንት ቅበላ ምጣኔ ከለውጡ በፊት ከነበው በሶስት እጥፍ መጨመሩን ጠቁመው÷ ወደ ምርት የገቡት ኢንቨስትመንቶች ፕሮጀክቶች ደግሞ በ66 በመቶ እድገት አሳይተዋል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ልኬት 61 በመቶ መድረሱን የገለጹት ኃላፊው÷ በዘርፉ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አንስተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች 187 ሺህ ቶን ምርት ወደ ውጪ ገበያ በመላክ 837 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አቶ አሕመድ ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይ በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀኑን ጠቁመው÷ ባለሃብቶች በተለይም ቢሾፍቱ፣ ሸገር እና አዳማ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመውሰድ መሬት አጥረው ያስቀመጡ፣ ወደ ልማት ያልገቡና የተሰጣቸውን ቦታ ለሌላ ዓላማ በሚያውሉ ባለሃብቶች ላይ ክትትል ተደርጎ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግም አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ