Fana: At a Speed of Life!

7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የዝግጅት ሥራዎች ተጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የዝግጅት ሥራዎችን ጀምሬያለሁ አለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ የቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም፤ ዝግጅቱ እየተከናወነ ያለው በ2018 ዓ.ም የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ መሠረት አድርጎ ነው ብለዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ባካሄደው ጥናት የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ፕላን ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡

ለቀጣዩ ምርጫ ግብዓት የሚሆኑ ተሞክሮዎችንና ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ የምርጫ ሂደቱን ከንክኪ የፀዳ ለማድረግም ውጥን ተይዟል ነው ያሉት፡፡

ምርጫ ጣቢያዎችን በአግባቡ መለየትና መቆጣጠር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለያዩ ክልሎች ወደ 12 ሺህ የሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎችን የማጣራት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች ፈተና በኦንላይን እንደሚሰጥ የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ በምርጫ ወቅት የእያንዳንዱን ባለሙያ እንቅስቃሴ የሚያመለክት ኦፕሬሽናል ማንዋል መዘጋጀቱ ገልጸዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መራጭ ብቻ ሳይሆን በዕጩነት መሳተፍ የሚችሉበት ጥናት መካሄዱንም አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ በፊት ዕጩዎች በምርጫ ክልል ብቻ ይመዘገቡበት የነበረውን አሠራር በማዕከል በኦንላይን መመዝገብ የሚያስችል መተግበሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ማበልጸግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

በአሸናፊ ሽብሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.