የገጠሩን ማሕበረሰብ አኗኗር ለማሻሻል የገጠር ኮሪደር በሁሉም አካባቢዎች እየተስፋፋ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገጠሩን ማሕበረሰብ አኗኗር ለማሻሻል የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት በሁሉም አካባቢዎች እየተስፋፋ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ዛሬ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ ሲንቢጣ ቀበሌ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆኑ ሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታን አስጀምረናል ብለዋል።
ሞዴል የገጠር መንደሮቹ ቀላል ወጪ የሚጠይቁ እና በአካባቢው በሚገኙ ግብዓቶች የሚገነቡ ሲሆኑ÷ አርሶ አደሩም ጤናማ እና ክብር ያለው ሕይወት እንዲኖር እንደሚስችሉ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ከ2 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ከዚህ ቀደም በጎርፍና ድርቅ አደጋ ይታወቅ የነበረውን አካባቢ የልማት ተምሳሌት ያደርገዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)።