Fana: At a Speed of Life!

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በጋራ ሊቆሙ ይገባል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር በጋራ ሊቆሙ ይገባል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ ለተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ባህል ግንባታ የፓርቲዎች ሚና በሚል መሪ ሐሳብ በመዲናዋ ከሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች፤ ኢትዮጵያውያን በጋራ በርካታ ጦርነቶችን በማሸነፍ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ቢችሉም፤ ከድል ማግስት ተቀራርቦ መወያየት ባለመቻሉ የፖለቲካ ቁርሾዎች መፈጠራቸውን አውስተዋል፡፡

በዚህም ፍላጎታቸውን ለማሳካት ትጥቅ ያነገቡ ኃይሎች መፈጠራቸውን እና ሀገር ብዙ ዋጋ መክፈሏን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የለውጡ መንግስት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጠናከር ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በዚህም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ አዲስ ምዕራፍ መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት በአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ በኃላፊነት እንዲሠሩ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የፖለቲካ ልዩነት ጤናማ መሆኑን በማመን መንግስት እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በጋራ እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡

በመድረኩ በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀሱ 17 የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች እና የአዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.