ሁዋጂያን በገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በሶላር ምርትና ኤክስፖርት ዘርፍ ሊሰማራ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይናው ሁዋጂያን ግሩፕ በገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለመሰማራት የ100 ሚሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን እና የሁዋጂያን ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ ዛንግ ሁዋሮንግ ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ሁዋጂያን ግሩፕ በሶላር ምርትና ኤክስፖርት ኢንቨስትመንት ዘርፍ በ100 ሚሊየን ዶላር በኢኮኖሚ ዞኑ የሚሰማራ ይሆናል፡፡
አቶ ሞቱማ ተመስገን ስምምነቱን አስመልክተው ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷በገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በተለያዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ለመፍጠር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የሃይል፣ መብራት፣ መንገድ፣ የውሃ፣ የግብዓት አቅርቦት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዛንግ ሁዋሮንግ በበኩላቸው ÷በኢትዮጵያ የተከናወነው የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያ ለኢንቨስትመንት መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
በገዳ ኢኮኖሚ ዞን በሶላር ምርትና ኤክስፖርት ዘርፍ ውጤታማ የልማት ሥራ ለማከናወን ቁርጠኛ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ሁዋጂያን በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ የመስሪያ ቦታ መረከቡን ጠቁመው÷ከሶስት ወራት በኋላ ሥራ እንደሚጀምር አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ