በአንድ ዘርፍ ላይ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያን ስብራት አይጠግንም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብዝሃ ዘርፍን ያላካተተና በአንድ ዘርፍ ላይ ጥገኛ የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ስብራት አይጠግንም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት፣ ወቅታዊ ፈተናዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች አስመልክቶ ባደረጉት ሁለተኛው ክፍል ልዩ ቃለ መጠይቅ ፥ የምናስበውን ብልጽግና ለማረጋገጥ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ለአገልግሎት ዘርፍ ያደላና ለአምራች ዘርፉ ትኩረት የሰጠ አይደለም በሚል የሚቀርቡ ሀሳቦች እውነትነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ ያሉ ችግሮችን በጥልቀት በመፈተሸ ባጠረ ጊዜና በመካከለኛ ጊዜ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ የኢኮኖሚ አማራጮችን በምዕራፍ በመክፈል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመለየት ሥራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡
በዚህም በየዘርፎቹ ያሉ እድሎችን እና አዋጭነታቸውን በመመርመር ዘላቂ ጥቅም ሊያስገኝ ለሚችል የኢኮኖሚ አማራጭ ቅድሚያ መሰጠቱን ነው ያብራሩት፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብዝሃ ዘርፍ ካልሆነና ብዝሃ ተዋንያንን ተጠቃሚ ማድረግ ካልቻለ በአንድ ዘርፍ ላይ ጥገኛ የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ስብራት እንደማይጠግንም አስገንዝበዋል፡፡
አንዱ ዘርፍ ሲደክም በሌላ በመተካካት ማስኬድ እስካልተቻለ ድረስ የሚታሰበው ብልጽግና ሊረጋገጥ አይችልም በሚል እሳቤ ለብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትኩረት መደረጉን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ዋና ግባችን ብልጽግናን በማምጣት ድህነትን መበቀልና ማጥፋት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የምናልመው ብልጽግና ያሉንን አማራጮች በጥልቀት ማወቅ ካልቻልን በአንድ ዘርፍ ብቻ ሊሳካ አይችልም ብለዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ያልታረሰ መሬት፣ የሰው ኃይልና የውሃ ሀብት መኖሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ በማረስ በምግብ ራስን መቻል ሁነኛ ጉዳይ በመሆኑ ልንተወው አንችልም ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በስፋት መስራት ካልተቻለ በግብርና ብቻ የሚታሰበውን የስራ እድል ፈጠራና የምርት አቅርቦት ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቱሪዝምና በማዕድን ያሉ እድሎችን መጠቀም የግድ መሆኑን ገልጸው፥ ነገር ግን ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ በቴክኖሎጂ ካልተደገፈ ብልጽግና የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ