Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያውያንን በሰፈር ሳይከፋፍል አቅፎ የያዘና የተለየ እሳቤ ያለው ፓርቲ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ የተለየ እሳቤ ያለውና ኢትዮጵያውያንን በሙሉ በሰፈር ሳይከፋፍል አቅፎ የያዘ ፓርቲ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአራተኛው ክፍል እና በመጨረሻው ቃለ ምልልሳቸው የብልጽግና ፓርቲ ቁመናን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ብልጽግና ተአምራዊ ፓርቲ መሆኑንና ከዚህ በፊት ከነበሩት በእሳቤ፣ በአደረጃጀት፣ በመጠን እና በሚያስገኛቸው ውጤቶች እንደሚለይ አስረድተዋል፡፡

ብልጽግና ከሁለተኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ የነበረው ስፋትና እድገት ጨምሮ አሁን ላይ 16 ነጥብ 3 ሚሊየን አባል ያለው ፓርቲ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ብልጽግና አካታችና አቃፊ ፣ ከብሄር ጽንፈኝነት የጸዳ እንዲሁም ለብሄራዊ ትርክት የሚተጋ እና ዳር የነበሩትንና የተረሱትን ወደ መሃል በማምጣት ለዴሞክራሲ ቀናኢ መሆኑን ያስመሰከረ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ በአፍሪካ ትልቁ ፓርቲ ሲሆን ÷ ሁሉን ያቀፈ፣ ካለው ስፋትና ትልቅ ራዕይ ባሻገር ግልጽ የሆነ አሰራርና ሥርዓት እንዲሁም እያንዳንዱ ፖሊሲዎች በመጽሐፍ መልክ የተገለጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የፓርቲው ስያሜም ከዚህ በፊት ከነበሩት በተለየ መልኩ ኢትዮጵያን የብልጽግና ማማ ላይ ለማድረስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ከተያዘው ራዕይ ጋር የተጋመደ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ብልጽግና የተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት ስልጣን ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረጉ ለሁሉም ዜጋ ክፍት መሆኑን ያረጋገጠበት ነው፤ ይህም የሁሉም አመራሮችና አባላት ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡

ፓርቲው ወጣቶችና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች አቅፎ የያዘ መሆኑን ጠቅሰው ÷ አዳዲስ እሳቤና አመለካከቶችን የመቀበል ችግር እንደሌለበት አመልክተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በብዙ መንገድ ተስፋ የሚጣልበት፣ የራሱ ሀገር በቀል እሳቤ ያለው እና በሌሎች ጉዳዮች በአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.