የ2017 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና መሰጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘንድሮ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የቅድመ ምረቃ የመውጫ ፈተና መሰጠት መጀመሩን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ፈተናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ በሚኒስቴሩ የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በ51 ዩኒቨርሲቲዎች በተዘጋጁ 87 የፈተና ማዕከላት ፈተናው እንደሚሰጥም ነው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የተናገሩት፡፡
በዚህ ዓመት እየተሰጠ ባለው የመውጫ ፈተና 190 ሺህ 787 ቅድመ ምረቃ ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 102 ሺህ 360 ተማሪዎች ፈተናውን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚወስዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ፈተናው በ238 የትምህርት መርሐ ግብሮች በሁሉም የፈተና መስጫ ማዕከላት በበይነ መረብ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ