Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የልማት ግቦቿን ከተባበሩት መንግስታት ግቦች ጋር በማስተሳሰር እየሰራች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት ግቦችን ከተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር እየሰራች ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

3ኛው ሀገር አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች የፈቃደኝነት የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለመተግበር ከወሰኑበት ጊዜ ጀምሮ በተቀመጠው የፈቃደኝነት ግምገማ አሠራር መሠረት ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ሪፖርት በማቅረብ ልምዷን አጋርታለች።

ለአብነትም በፈረንጆቹ 2017 ድህነትን ማጥፋትና ብልጽግናን ማስፋፋት በሚል ዋና ርዕስ በተዘጋጀው የፈቃደኝነት ግምገማ ላይ ሪፖርት አቅርባ ተሞክሮዋን ለሌሎች ሀገራት እንዳካፈለች አስታውሰዋል፡፡

ከመድረኩ ጠቃሚ ግብረ መልሶች እና ልምዶች መገኘታቸውንም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

በሁሉም አባል ሀገራት እየተተገበረ የሚገኘው የዘላቂ ልማት አጀንዳ 2030 የማይነጣጠሉና ሁሉን አቀፍ ባህሪያት ያሏቸው 17 ግቦችን፣ 169 ኢላማዎች እና 230 አመልካቾችን ያካተተ ነው፡፡

ይህ የልማት አጀንዳ ሕዝቦችን ከድህነትና ከረሃብ ለማላቀቅ፣ መሬትን ከጥፋት ለመታደግና የሰው ልጆችን የተሟላ ኑሮና ብልፅግና ለማረጋገጥ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

በዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት በሚካሄደው የፈቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማ ላይ ኢትዮጵያ ለሶስተኛ ጊዜ ለማካሄድ ለተባበሩት መንግስታት ፈቃደኝነቷን ገልጻ ይሁንታ አግኝታለች ፡፡

በዚህ መሰረትም የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ የ2025 የዘላቂ ልማት የፈቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማ ለ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ ዘላቂ፣ አካታች፣ ሳይንሳዊና በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎችና ዘላቂ ልማት ለሁሉም በሚል ዋና ጭብጥ ሪፖርቱን አዘጋጅታለች።

ግቦቹ ጤናማ ሕይወትን ማረጋገጥና ደህንነትን ለሁሉም በሁሉም የዕድሜ ክልል ማስፋፋት፣ የጾታ እኩልነትን ማረጋገጥና ሁሉንም ሴቶችና ልጃገረዶች በተሟላ ሁኔታ ማብቃት፣ አካታችና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም የተሟላና ፍሬያማ የሆነ ምቹ ሥራን ለሁሉም ማስፋፋት ላይ ያተኩሩ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የውሃ ሥነ-ምህዳርን ለዘላቂ ልማት መጠበቅ እና ለዘላቂ ልማት ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ማጠናከር ላይ በማተኮር ሁሉንም የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም በማካተት እንደተዘጋጁ ተጠቁሟል፡፡

የሪፖርት ዝግጅቱ የተገኙ ቁልፍ ስኬቶችን በመለየት ስኬቶቹ እንዴት እንደተገኙ እና ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮች በቀጣይ እንዴት እንደሚፈቱ የመፍትሄ ሃሰብ ለማመላከት እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮዋን ማካፈል እንድትችል ያለመ ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ሊጠናቀቅ አምስት ዓመታት በቀሩት የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸም ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ለሀገራት እያጋራች መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ የተቀመጡ የልማት እቅድና ግቦች ሀገራዊ ልማትን ማሳካት በሚቻልበት መልኩ እየተተገበሩ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡

የስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የኮሪደር ልማት ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና መሰል የልማት አጀንዳዎች የትግበራው አካል እንደሆኑም ተናግረዋል።

በለይኩን ዓለም

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation

Facebook FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)

Telegram t.me/fanatelevision

Website www.fanamc.com

TikTok www.tiktok.com/@fana_television

WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29

Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment

Facebook WMCC

TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment

Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.