Fana: At a Speed of Life!

ፌዴሬሽኑ ለግብርና ሥራ የሚያስፈልጉ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ኬሚካሎችን እያቀረበ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ የግብርና ህብረት ስራ ማህበራት ፌዴሬሽን ለግብርና ሥራ የሚያስፈልጉ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ኬሚካሎችን ለአርሶ አደሮች እያቀረበ ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ተሾመ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ የአርሶ አደሩን የግብርና እንቅስቃሴ እና ህይወት ለመቀየር የተቋቋመው ማህበሩ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ከ7 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችን በማስተባበር የግብዓት አቅርቦቶችን የሚሰጠው ፌደሬሽኑ በተለይም ለግብርና ሥራ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎች እና መድኃኒቶችን ለአርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ከፍተኛ ጥራት ያላቸው እና ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ ኬሚካሎች በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት ከ3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ኬሚካሎችን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው÷ በአሁኑ ወቅት ግብዓቶቹን የማከፋፈል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኬሚካሎቹ በዋናነት የፀረ አረም፣ የፀረ በሽታ እና የፀረ ተባይ መድኃኒቶች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አለማየሁ÷ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ኬሚካሎቹ ከመከፋፈላቸው በፊት ለአርሶ አደሮች የአጠቃቀም ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ በቂ አቅርቦት በመኖሩ አርሶ አደሩ ግብዓቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.