የአርሜኒያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፕሬዚዳንት ታዬ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአርሜኒያ ባለሃብቶች የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም እድሎች በመጠቀም ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የአርሜኒያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫሃን ኮስታኒያን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ከአርሜኒያ ፕሬዚዳንት ቫሃግን ካቻቱሪያን የተላከ መልዕክት ለፕሬዝዳንት ታዬ አቅርበዋል።
በውይይታቸውም፤ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በባህልና በትምህርት ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ ሀገራቱ ጥልቅና ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው በማውሳት ግንኙነታቸውን በተለያዩ የትብብር መስኮች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም እያደረገች ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የአርሜኒያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቫሃን ኮስታኒያን በበኩላቸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደምትሠራ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡