Fana: At a Speed of Life!

ቋንቋ በሕዝቦችና ባህሎች መካከል ድልድይ ነው – የሩሲያ አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ ቋንቋ ቀን በአዲስ አበባ በተባበሩት መንግሥታት የስብሰባ ማዕከል ተከብሯል፡፡

በዝግጅቱ ሩሲያዊው የኪነ-ጥበብ ሊቅ እና የሩሲያ ዘመናዊ ሥነ-ጽሑፍ አባት እንደሆነ የሚነገርለትን አሌክሳንደር ሰርጌቪች ፑሽኪንን ጨምሮ የኒኮላይ ጎጎልና መሰል ዝነኛ የሩሲያ የጥበብ እና የፍልስፍና ሥራዎች ተዘክረዋል።

በተጨማሪም የሩሲያን ጥበብ እና ባህል የሚያሳይ የሥዕል ዐውደ-ርዕይ ቀርቧል፡፡

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን በዚሁ ጊዜ፤ የፑሽኪን እና የኢትዮ-ሩሲያ የሕዝብ-ለሕዝብ ግንኙነትን አውስተው፤ ኢትዮጵያ ለሩሲያውያን ታላላቅ የጥበብ ሰዎች እና ፈላስፋዎች ከፍ ያለ ቦታ እንዳላት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህልና ታሪክም በብዙኃኑ ታዋቂ የሩሲያ ምሁራን እና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

ቋንቋ በሕዝቦችና ባህሎች መካከል ድልድይ መሆኑን ገልጸው፤ ከመግባቢያነት ባለፈ ሰዎችን የሚያገናኝ እና ታሪክን የሚጠብቅ ሀብት ነው ብለዋል፡፡

በሀገራቱ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ የሕዝብ ለሕዝብ እና የባህል ትስስር እንዲጎለብት ካደረጉት መካከል ፑሽኪን አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮ-ሩሲያ ግንኙነትን በይበልጥ ለማሳደግ የቋንቋ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራቸው ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የምትሰጠው የትምህርት ዕድልም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ የሳይንስ እና የባህል ማዕከል ቋንቋውን ለመማር ፍላጎት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እየደገፈ መሆኑም አስታውቀዋል፡፡

ዛሬ ታስቦ የዋለው የሩሲያ ቋንቋ በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል እያደገ የመጣውን የባህል እና የትምህርት ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ነው ያስረዱት፡፡

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሣይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተወካይ ሪታ ቢሶኖዝ በበኩላቸው፤ የሩሲያ ቋንቋ ከተባበሩት መንግሥታት የሥራ ቋንቋዎች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ድርጅታቸው የሩሲያ ቋንቋን ጨምሮ በዓለም ላይ ያሉ ሌሎች ቋንቋዎችና ባህሎች ኅልውናቸው አንዲጠበቅ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ባለድርሻ አካላትም ለሁሉም ቋንቋዎች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርጉ ጠይቀው፤ ዓለማችን ብዝኃ-ቋንቋን ያለአድልኦ የምታስተናግድ እንድትሆን የድርጅታቸው ግብ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመሳፍንት ብርሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.