ቻይና የደቡብ ሀገራት ለጋራ እድገት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና በማደግ ላይ የሚገኙ የደቡብ ሀገራት ለጋራ ራዕይ እና እድገት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቀረበች፡፡
ቻይና ከአፍሪካ እና ደቡብ ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር የደረሰችውን የቻንግሻ ስምምነት አፈጻጸምን አስመልክቶ የጋራ ምክክር ተደርጎ የቻይና መንግስት እና የ53 አፍሪካ ተወካዮች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር÷ በውይይቱ የደቡብ ሀገራት የጋራ ራዕይ የዓለምን ቀጣይ እጣ ፋንታ የሚወስን በመሆኑ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ከስምምነት መደረሱን ገልጿል።
የደቡብ ሀገራት ኢኒሼቲቭ በሆነው የቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት፣ በዓለም አቀፍ የደህንነት እና የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ኢኒሼቲቮች ላይ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቋል፡፡
በአንድ ዋልታ የሚቆም የአኮኖሚ እና ፖለቲካ ዓለም መፈጠር የታዳጊ ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴን ተፅዕኖ ውስጥ የሚከት በመሆኑ የደቡብ ሀገራት ለባለብዙ ዋልታ ዓለም መፈጠር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም የጋራ አቋም ተይዟል፡፡
ሀገራት የታሪፍ ምጣኔያቸው በእኩልነት፣ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መወሰን እንዳለባቸው ተነስቷል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች በበኩላቸው÷ ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት ሉዓላዊነት፣ እኩልነት እና ፍትህ መረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
በተጨማሪም ቻይና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ስርዓትን ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም የውጭ ጫናዎችን ለመከላከል የያዘችው አቋም የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የዓለም ንግድ ስርዓት የአፍሪካ እና ደቡብ ሀገራትን ያሳተፈ እንዲሆን ለማድረግ በትብበር መስራት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
የቻይና እና አፍሪካ ግንኙነት በአረንጓዴ ልማት፣ በኢ-ኮሜርስ እና ኢ-ፔይመንት፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በፀጥታ እና ደህንነት፣ በፋይናንስ እና ሌሎች ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ