ብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሸስ ጁኒየር …
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዘመን ቅብብል በእግር ኳስ ችሎታቸው እና ክህሎታቸው የእግር ኳስ ቤተሰብን የሚያዝናኑ እና ቀልብን የሚስቡ ከዋክብቶች ለዓለም ስታበረክት የቆየችው ብራዚል በአሁኑ ዘመን ካፈራቻቸው ከዋክብቶች መካከል ይጠቀሳል ቪኒሸስ ጁኒየር፡፡
ቪኒሸስ ጁኒየር በእግር ኳስ መድረክ ለመንገስ እና ለመድመቅ በክለቡ ሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ጭምር ተፈትኗል። ሪያል ማድሪድን ከተቀላቀለ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ወጥ ብቃት ማሳየት ባለመቻሉ ቡድኑን መላመድ ከብዶት ነበር።
ነገር ግን ከቆይታዎች በኋላ ሪያል ማድሪድን በመላመድ ወደ ድንቅ ብቃቱን ለማሳየት በቅቷል። በዚህም ሪያል ማድሪድ በሚፈተንባቸው ወሳኝ ጨዋታዎች በቪኒሸስ ጁኒየር አማካኝነት ወደ አሸናፊነት ይመጣል።
ለአብነትም በ2022 የውድድር ዘመን ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን አሸንፎ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ሲያሳካ የላቀ ሚና የነበረው ቪኒሸስ ጁኒየር ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል።
በየጊዜው የሚሰነዘርበት የዘረኝነት ጥቃት ለእሱ ከፈተናዎቹ ሁሉ ትልቁ ፈተናው ቢሆንም በሜዳ ላይ ብቃቱን ከማሳየት፣ ጎል ከማስቆጠር፣ ዋንጫዎችን ከማሳካት እንዲሁም በቡድኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጨዋች ከመሆን አላገደውም።
ቪኒሸስ ጁኒየር የሚሰነዘርበትን የዘረኝነት ጥቃት የወጣትነት ጫንቃው መሸከም ቢያቅተው የመጫወቻ ሜዳውን ለቅቆ በመውጣት ወደ መልበሻ ክፍል ለመግባት ተንደርድሯል፤ አንባ አውጥቶ አልቅሷል።
አሁን ምስጋና ለተዓምረኛ እግሮቹ እና ድንቅ ችሎታው ይሁንና በክለቡ ሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ገብቷል፡፡
በየጨዋታው የሚጮኹበትን የሌላ ክለብ ደጋፊዎችን ተፅዕኖ ተቋቁሞ በሎስብላንኮቹ ቤት የሪያል ማድሪድን ሀያልነት ከአንጋፋ ኮከቦች ተረክቦ እያስቀጠለ የሚገኝ ድንቅ ኮከብ ነው፡፡ በፍጥነቱ፣ ክህሎቱ እና እልኸኝነቱ ለተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች ፈታኝነቱ ቀጥሏል።
በፈረንጆቹ 2024 የፊፋ የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ተብሎ ሲመረጥ በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ “የመጣሁት ለመኖር አስቸጋሪ ከሆነ ትንሽ መንደር ነው፣ ድህነት እና ወንጀል ከተንሰራፋበት፤ በሳሆ ጎንሳሎ ጎዳና በባዶ እግሬ ስጫወት እዚህ መድረስ የማይቻል ይመስለኝ ነበር” ብሎ በመናገር ለስኬት የደረሰበት መንገድ ምን ያህል ፈታኝ እንደነበር አስታውሷል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ