Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የባህልና የእውቀት ማዕከል እየሆነች መታለች – አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መዲና ከመሆን አልፋ የባህልና የእውቀት ማዕከል እየሆነች መታለች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርሃኑ ፀጋዬ።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት “ኢትዮጵያ በዲፕሎማቶች እይታ” የተሰኘ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ ዛሬ ማምሻውን በአዲስ አበባ ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በተከፈተበት ወቅት ነው።

ዐውደ ርዕዩ “አብሮነት፣ ብዝኃነትን እና መግባባትን መዘከር” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ ሲሆን÷ ዲፕሎማቶች በመላው ኢትዮጵያ ባደረጉት የመስክ ጉብኝት ወቅት ያነሷቸው ፎቶግራፎች ቀርበዋል።

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በዚሁ ወቅት÷ ዐውደ ርዕዩ ኢትዮጵያን በውጭ ዲፕሎማቶች መነፅር ብቻ ሳይሆን በወዳጆቻችን እይታ እንድንመለከት የሚጋብዝ ነው ብለዋል።

ምስሎቹ የኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ ባህላዊ ቅርሶች፣ የተለያዩ መልከዓ ምድሮች እና የህዝቦቿን የህበረ ብሔራዊነትና አብሮነት መንፈስ የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ ከኒውዮርክ እና ጄኔቫ በመቀጠል በዓለም ሦስተኛዋ ትልቁ የዲፕሎማቲክ ማዕከል መሆኗን ገልጸው÷ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መዲና ከመሆን አልፋ የባህልና የእውቀት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።

የመዲናዋ ያልተቋረጠ እድገት በኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቭና ሌሎች ዋና ዋና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት እየተፋጠነ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው÷ ከተማዋ ዘመኑን የምትመጥን፣ ፅዱ እና አረንጓዴ ከተማ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትጵያን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው አስበው ያላቸውን ክብርና ፍቅር ስላሳዩ የተሳተፉትን የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትን እንዲሁም የፎቶ አውደ ርዕዩን በማዘጋጀት እና በማስተባበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ዝግጅቱን ያስተባበሩት የሞሮኮ፣ ሮማኒያ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ኢንዶኔዥያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኤምባሲዎች እና የዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቢሮ መሆናቸው ተገልጿል።

ከፎቶግራፎቹ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ባለተሰጥኦ ኢትዮጵያዊን ወጣት የጥበብ ባለሙያዎችን ለመደገፍ ይውላል ተብሏል።

የፎቶ ዐውደ ርዕዩ ከሰኔ 6 እስከ 18 ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ተመላክቷል፡፡

በመሳፍንት ብርሌ

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.