Fana: At a Speed of Life!

የክለቦች የዓለም ዋንጫ …

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር ወደ 32 ከፍ በማድረግ ዳጎስ ያለ ሽልማት ይዞ በአዲስ የውድድር ቅርጽ የተመለሰው የክለቦች የዓለም ዋንጫ ዛሬ ሌሊት ይጀምራል፡፡

በአሜሪካ በተሰናዳው የክለቦች ዓለም ዋንጫ 12 የአውሮፓ ክለቦችን ጨምሮ ከሁሉም አህጉራት በአጠቃላይ 32 ክለቦች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

በፈረንጆቹ 2000 የተጀመረው የፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫ የአህጉራዊ ውድድሮች አሸናፊዎችን ተሳታፊ በማድረግ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

በዚህ ዓመት የውድድሩን ቅርጽ በማሻሻል፣ የተሳታፊዎችን ቁጥርና የሽልማት መጠን በማሳደግ በተለየ ሁኔታ ይካሄዳል፡፡

ሪያል ማድሪድ፣ ቼልሲ ፤ማንቼስተር ሲቲ፣ ባየርን ሙኒክ፣ ፒኤስጂ፣ ኢንተር ሚላን፣ ፖርቶ፣ ቤኔፊካ፣ ቦርሲያ ዶርትሙንድ፣ ዩቬንቱስ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ እና አርቢ ሳልዝበርግ በውድድሩ የሚሳተፉ የአውሮፓ ክለቦች ናቸው፡፡

አራቱ የብራዚል ክለቦች ፍሉሚኔንስ፣ ፓልሜራስ፣ ፍላሚንጎ እና ቦታፎጎ እንዲሁም ሁለቱ የአርጀንቲና ባላንጣ ክለቦች ቦካ ጁኒየርስ እና ሪቨር ፕሌት ላቲን አሜሪካን ይወክላሉ፡፡

የግብጹ አል አህሊ፣ የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ፣ የቱኒዚያው ኢስፔራንስ ዲ ቱኒዝ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከአፍሪካ የተወከሉ ክለቦች ናቸው፡፡

በተመሳሳይ በመድረኩ በአራት ክለቦች የተወከለው የእስያ አህጉር የሳዑዲ ፕሮ ሊጉን አልሂላል፣ የጃፓኑን ኡራዋ ሬድ ዳይመንድስ እንዲሁም የደቡብ ኮሪያውን አልሳን ኤችዲ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን አል አይን ያሳትፋል፡፡

ሞንቴሪ፣ ሲያትል ሳውንደርስ፣ ፓቹካ እና ኤል ኤ ኤፍ ሲ የሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካን ሲወክሉ፥ የኒውዚላንድ ክለብ የሆነው ኦክላንድ ሲቲ የኦሺኒያ ተወካይ ሆኖ በውድድሩ ይሳተፋል።

በውድድሩ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች የተመረጡት በዋናነት ከ2020/21 እስከ 2023/24 ባሉት የውድድር ዓመታት በአህጉራዊ መድረክ በነበራቸው ውጤት መሆኑን ፊፋ ገልጿል።

ሊዮኔል ሜሲን የያዘው የሜጀር ሊግ ሶከሩ ኢንተር ማያሚ ሌላኛው የውድድሩ ተሳታፊ ክለብ ነው፡፡

ዛሬ ሌሊት 9 ሰዓት የሚጀምረው የክለቦች የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ አስተናጋጅነት ለአንድ ወር ያህል ሲቆይ በመክፈቻው ኢንተር ማያሚ ከአል አህሊ ጋር ይገናኛሉ።

ውድድሩ በስምንት ምድብ ተከፍሎ የሚደረግ ሲሆን፥ ከየምድቡ 1ኛ እና 2ኛ በመሆን የሚያጠናቅቁ ክለቦች ጥሎ ማለፉን ይቀላቀላሉ።

ፊፋ ከአሁን ቀደም በ2023 በተደረገው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ለሽልማት ክፍያ የመደበው በጀት 16 ሚሊየን ዶላር ብቻ የነበረ ሲሆን፥ ዛሬ ሌሊት ለሚጀምረው የ2025 የክለቦች ዓለም ዋንጫ 1 ቢሊየን ዶላር አዘጋጅቷል።

በየዓመቱ ሲካሄድ የነበረው የክለቦች ዓለም ዋንጫ እንደ ሀገራት ዓለም ዋንጫ ከዚህ አመት ጀምሮ በ4 ዓመት አንድ ጊዜ ይደረጋል።

ፊፋ አዲሱን የውድድር ቅርጽ ይፋ ካደረገ በኋላ በተለይም ተጫዋቾች በቂ የእረፍት ጊዜ እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው የሚል ትችቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።

ነገር ግን ተሳታፊ ክለቦች ከውድድሩ ዳጎስ ያለ ክፍያ ስለሚያገኙ በውድድሩ ላይ ቅሬታ ከማሰማት ተቆጥበዋል።

በኃይለማሪያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.