ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ስምና ክብር በዓለም ከፍ ለማድረግ ሊተጋ ይገባል – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ የኢትዮጵያን ስምና ክብር በዓለም ከፍ ለማድረግ ሊተጋ ይገባል አሉ፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምሥረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በ4 ቢሊየን ብር ወጪ ያስገነባቸውን 22 ፕሮጀክቶች አስመርቋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፥ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ለአንድ ምዕተ ዓመት ለአካባቢው ማህበረሰብ የሕክምና አምባ፣ የመዳንና የመጠገን ምልክት ከመሆኑም ባሻገር ስመጥር ባለሙያዎችን ያፈራ የልህቀት ማዕከል መሆኑን ተናግረዋል።
ከ70 ዓመታት በፊት የተለኮሰው የዩኒቨርሲቲው የእውቀትና የትምህርት ጉዞ ደግሞ ለሀገራችን መድህን የሆኑ መፍትሔዎችንና ዜጎችን ማፍለቅ መቻሉን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲተው ከ10 ዓመት በፊት ከሚያውቁት የላቀና የሚያኮራ ለውጥ ማስመዝገቡን ነው ፕሬዚዳንቱ አጽንኦት የሰጡት።
ስኬቱም የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና የማህበረሰቡ በሥራ የመግባባት ያመጣው መሆኑን በማንሳት፥ የጀመረውን የዘመናዊነት ፈር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የጎንደር ማህበሰብ ለዩኒቨርሲቲው ያለው ልዩ የባለቤትነት ስሜትና ለኢትዮጵያውያን የአንድነት ጉዞ ልዩ ምሳሌ የሚሆንና የስኬቱ ሚስጢር እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ማህበረሰቡ ለተቋሙ ቀጣይነት ያለው ለውጥ የሰጡት ትኩረት ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት የመሸጋገር የዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ ሆኖ የጀመራቸው ሥራዎች ተቋሙን ወደላቀ ከፍታ የሚያሸጋግሩ እንደሆኑ መጥቀሳቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።