ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ አቻ ተለያዩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 35ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ሶስት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡
በሊጉ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች የተሳተፉባቸው ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9 ሰዓት ላይ ነው የተካሄዱት፡፡
በዚህ መሰረትም አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቅቋል።
የአዳማ ከተማን ግቦች ነቢል ኑሪ እና አድናን ረሺድ ሲያስቆጥሩ÷ የፋሲል ከነማን ደግሞ ጌታነህ ከበደና አንዋር ሙራድ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡
በተመሳሳይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ይድነቃቸው ተሰማ የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ አካዳሚ በተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ መቻልን 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡
በተጨማሪም በወንጂ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።