Fana: At a Speed of Life!

በስንዴ የተገኘውን ውጤታማነት በሌሎች ምርቶች ለመድገም በትኩረት መስራት ይገባል – ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እና የምግብ ሥርዓትን ለመገንባት የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ማጠናከር ይገባል አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡

የግብርና ሚኒስትር አማካሪ አቶ ዜና አበበ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያ የማይበገር እና ዘላቂነት ያለው የግብርና እና የምግብ ሥርዓትን ለመገንባት የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ እየሰራች ነው፡፡

ለአብነትም በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በሩዝ ምርት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና በሌሎች ኢኒሼቲቮች አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

የግብርና ዘርፍ ለኢኮኖሚ እድገት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመው ÷ ለዚህም መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ሀገራዊ ፍጆታዋን በሀገር ውስጥ ምርት በመሸፈን ከውጭ የሚገባውን ማስቀረቷን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ በስንዴ የተገኘውን ውጤታማነት በሩዝ ምርትና በሌሎች ለመድገም በትብብር እንደሚሰራ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ለሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ እንዲሁም የምግብ ዋስትናንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካዳፕ) ግቦችን ለማሳካት በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ አብራርተዋል፡፡

በዘርፉ የሚገኙ የአፈጻጸም መረጃዎችን እና ሪፖርቶቸን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ዘርፍ አፈጻጸም መረጃዎችን ከፕላንና ልማት፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ሌሎች ተቋማት ጋር የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም ግቦችን ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት የዓለም ባንክ፣ ኢጋድና ሌሎች አጋር አካላት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.