በጎንደርና ባሕርዳር የተገነቡ ፕሮጀክቶች ትውልዱ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ያሳያሉ – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎንደር እና ባሕርዳር ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የአሁኑ ትውልድ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ያሳያሉ አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
ፕሬዚዳንት ታዬ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጎንደርና ባሕርዳር የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ ጉብኝቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ ጎንደር ታሪኳን በጠበቀ መልኩ በኪነ ሕንጻዎቿ ሥራ ለዚህ ዘመን አበርክቶ እንዲኖራት የተሰሩ ሥራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በጎንደር ሰላምና ልማት እየተረጋገጠ መሆኑን ያሳያሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ ÷ በከተሞች እየታየ ያለው ልማት የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
በተመሳሳይ የባሕርዳር ዓባይ ድልድይን ጨምሮ በከተማዋ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ወደ ልዩና አዲስ የከተሜነት ምዕራፍ እንደሚያሸጋግራት አንስተዋል፡፡
የባሕር ዳር ስታዲየም ለከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴና ውድድሮች ከሚሰጠው ጥቅም ባለፈ አህጉራዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት እንደሚያስችል ጠቁመው ÷ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ትጋት አድንቀዋል።
በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፡፡
በለይኩን ዓለም