Fana: At a Speed of Life!

ኢራን እና እስራኤል ጥቃት መሰናዘራቸውን ቀጥለዋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እየተባባሰ በመጣው የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ኢራን በደቡባዊ እስራኤል በምትገኘው የቢርሼባ ከተማ የሚሳኤል ጥቃት ፈፅማለች፡፡

በጥቃቱ በከተማዋ የሚገኘው ሶሮካ ሆስፒታል ኢላማ መደረጉ በእስራኤል በኩል የተገለጸ ሲሆን፤ 30 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የእስራኤል አስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት ገልጿል።

ኢራን በበኩሏ ዛሬ የፈጸመችው ጥቃት ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ ያደረገ መሆኑን በመግለጽ፤ ከሆስፒታሉ አቅራቢያ በሚገኝ ወታደራዊ ተቋም እንጂ በሆስፒታሉ ላይ ጥቃት አለመሰንዘሩን በመጥቀስ የኢራን መገናኛ ብዙሃኖች ዘግበዋል።

እንደ ኢራን ዜና አገልግሎት ዘገባ፤ ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው በጋቭ-ያም ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ የሚገኘውን የእስራኤል መከላከያ ሃይል የዕዝ እና ደህንነት ዋና መስሪያ ቤትን ነው።

በመሆኑም በአቅራቢያው የሚገኘው ሆስፒታል መጠነኛ ጉዳት ያጋጠመው በወታደራዊ ተቋሙ ላይ የተፈጸመው ፍንዳታ ባስከተለው ከፍተኛ ንዝረት እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ኢራን በእስራኤል ላይ ለፈጸመችው ጥቃት ዋጋ እንደምትከፍል ገልጸዋል።

በተመሳሳይ እስራኤል ዛሬ ማለዳ ባደረገችው ዘመቻ አራክ እና ናንታዝ በተባሉት የኢራን የኑክሌር ማመንጫ ስፍራዎች ላይ የተሳካ ጥቃት መፈፀሟን አስታውቃለች፡፡

ሁለቱ ሀገራት የእርስ በርስ አፀፋ እየተሰጣጡ ባለበት በዚህ ሰዓት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ጦርነቱን ልትቀላቀል እንደምትችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሀሚኒ÷ አሜሪካ ጣልቃ የምትገባ ከሆነ ከፍተኛ አደጋ ሊከተል እንደሚችል ማስጠንቀቃቸው ይታወቃል።

የሁለቱ ሀገራት ሁኔታ እየከፋ መምጣት ዓለምን ወደ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ የሚከት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግስታት ሀገራቱ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.